መንግስት የመጠባበቂያ ክምችት እየተጠቀመ ስለሆነ ኢትዮጵያውያን ነዳጅ እንዲቆጥቡ ጥሪ አቀረበ
ሀገሪቱ ከመካከለኛው ምስራቅ በቂ አቅርቦት ለማግኘት እየሞከረች ባለበት ወቅት ዜጎቿ በነዳጅ አጠቃቀም ረገድ ቆጣቢ እንዲሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አሳሰቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሰኞ እለት በኤክስ ገጻቸው ላይ ይህ ሁኔታ መፍትሄ እስኪያገኝ እና የተለመደው የነዳጅ አቅርቦት ስርዓት እስኪመለሰ ድረስ ነዳጅ መቆጠብ እና ለመሰረታዊ እና አስፈላጊ ፍላጎቶች ቅድሚያ መስጠት አስፈላጊ ነው ብለዋል። ነዳጅ አከፋፋዮች እና ሸማቾችም ለአስፈላጊ አገልግሎቶች ቅድሚያ እንዲሰጡ እና ነዳጅን በኃላፊነት እንዲጠቀሙ ጠይቀዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋን በመደጎም የዋጋ ንረትን ለመቀነስ እና ለገቢ ዕቃዎች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ መመደቧን ገልፀዉ በተለይም በሆርሙዝ የባህር ዳርቻ አካባቢ በተከሰተው የአቅርቦት መስመር መቆራረጥ ምክንያት ወጥ የሆነ አቅርቦት እንዲኖር በ13 ቦታዎች የተያዙ አንዳንድ ክምችቶችን እየለቀቀች ነው ብለዋል ።
በቅርቡ ይፋ በሆነው መረጃ መሠረትም በ2023-24 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ 3.93 ሚሊዮን ቶን (4.8 ቢሊዮን ሊትር) የተጠቀመች ሲሆን፣ ከዚህም ሩብ ያህሉ ለአህጉሪቱ ዋና የአየር ትራንስፖርት ማዕከል የአቪዬሽን ነዳጅ እንደነበር መረጃው ያመላክታል።
ኢትዮጵያ አቅርቦቱ ከመቋረጡ በፊትም በእጥረት እየታገለች የነበረ ሲሆን፣ ይህም በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሽያጭ ላይ ከፍተኛ እድገት እንዳስከተለ የሚታወቅ ነው።