Home News Business
Business

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የስድስት ወራት አጠቃላይ ሽያጭ 65.99 ቢሊየን ብር ማከናወኑን ገለጸ

March 10, 2026 5 days ago

‎ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የ2017/2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸሙን በሸራተን አዲስ ሌግዠሪ ኮሌክሽን ሆቴል ገምግሟል።

በግምገማዉም ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በ2017/2018 የበጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ 65.99 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ሽያጭ ሪፖርት ያደረገ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ71 በመቶ ጭማሪ እንዲሁም ከትርፍ አንጻርም የእቅዱን 176 በመቶ በማሳካት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ95 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ ሪፖርቱ አመላክቷል።

ሚድሮክ በግማሽ አመቱ ለግብርና እና ለሌሎች መንግስታዊ ግዴታዎች ከ18.4 ቢሊዮን በላይ ያወጣ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ166 በመቶ ጭማሪ እንዲሁም ለአለም አቀፍ ገበያዎች ከሚያቀርባቸው ምርቶች እና አገልግሎቶች ከ155 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ በማግኘት ካለፈው የበጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም የ53 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ መግለጫዉ አመላክቷል። በተጨማሪም ቡድኑ በበጀት አመቱ ስድስት ወራት ለሰራተኛ ደሞዝ ክፍያ ከ4.5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማደረጉንም በሪፖርቱ ተገልጿል።

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ጀማል አህመድ ሚድሮክ በሁሉም ዘርፎች በከፍተኛ ጥራት ሀገሪቱን የሚያኮሩ ፕሮጀክቶች ላይ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ያገኘው ውጤት አበረታች መሆኑን ገልጸው በሁሉም ዘርፎች ማለትም በማርኬቲንግ፣ በግብይት፣ በምርት እና በወጪ ቅነሳ ላይ ማተኮር አስፈላጊ መሆኑንም አፅንዖት ሰጥተዋል። ቀጥለውም ኩባንያው የአተገባበር እና የአሠራር ስርዓቶችን በማዘመን ቀጣይነት ያለው ተቋማዊ ውጤታማነትን የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ያደርጋልም ብለዋል።

ዋና ሥራ አስፈፃሚውም ግሩፑ በተያዘው በጀት አመት እጅግ ግዙፍ የሆኑ አዳዲስ ፕሮጀክቶች የጀመረ መሆኑን ገልጸው በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀውም አገልግሎት እንዲሰጡ እና ግሩፑም በሀገር ዉስጥና በዓለም ገበያ ያለዉን ድርሻ በማሳደግ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም የግሩፑ አመራር በባለቤትነት ስሜት እንዲንቀሳቀስ አሳስበዋል።

‎ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በስድስት ዘርፎች የተደራጁ ከ45 በላይ የሚሆኑ ድርጅቶችን በስሩ ያቀፈ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ80 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር የቻለ ግዙፍ ተቋም ነው።

Scroll to Top