በአህጉሪቱ ዓለም አቀፍ የንግድ ተወዳዳሪነትን ለማምጣትና የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማፋጠን፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን ሙሉ በሙሉ መተግበር ይገባል
በአህጉሪቱ ዓለም አቀፍ የንግድ ተወዳዳሪነትን ለማምጣትና የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማፋጠን፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን(AfCFTA) ሙሉ በሙሉ መተግበር እንደሚገባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ክላቨር ጋቴቴ ገለጹ።
የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም 2026 "የአፍሪካን የወደፊት ተስፋ በገንዘብ መደገፍ፣ የሥራ ዕድልና ኢኖቬሽን ለዘላቂ ሽግግር" በሚል መሪ ሀሳብ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እየተካሄደ ነው።
የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ክላቨር ጋቴቴ በዚሁ ወቅት፤ አፍሪካ ሁሉን አቀፍ ሽግግር ለመጀመር ዝግጅት ላይ ሳትሆን ቀደም ብላ ወደ ሂደቱ መግባቷን ገልጸዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ሕዝብን ያቀፈ አንድ የገበያ ማዕከል የፈጠረ መድረክ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም የዲጂታል ግብይት ሥርዓት መስፋፋትና የስታርታፕ ንቅናቄ ማደግ ለዚህ ማሳያ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ያለውን የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት በምሳሌነት ያነሱት ዋና ጸሐፊው፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ነጋዴዎችና ኤጀንቶች እየተሳተፉበት ያለው ይህ ሥርዓት የአፍሪካ ሽግግር በተግባር እየታየ መሆኑን ያረጋግጣል ብለዋል።
አፍሪካ በዓለም የንግድ ሥርዓት ንቁ ተሳታፊ ለመሆን የውስጥ የገቢ አቅምን ማሳደግ፣ ፈጠራን ማዕከል ያደረጉ የፋይናንስ መሣሪያዎችን ማሰማራት እንዲሁም ነፃ የንግድ ቀጣናውን ወደ ሙሉ ትግበራ ማሸጋገር እንዳለባት ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በፖሊሲ ትንተና፣ በትብብርና በሌሎችም መስኮች አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ዋና ጸሐፊው አረጋግጠዋል።